በሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ ወረዳ በ88 ሚሊዮን 28 ሺህ 108 ብር ወጪ የተገነባው የአጆ ሜዳ 1ኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታው ተጠናቆ ተመረቋል።
ትምህርት ቤቱ በዓለም ባንክ እና በፌዴራል ከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔትና ሥራ ፕሮጀክት የገንዘብ ድጋፍ የተገነባ ሲሆን፣ 9 ብሎኮችን ያካተተው ይህ ግንባታ በጥራትና በ5 ወራት አጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑ ተገልጿል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የሰሜን ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ታምራት ንጋቱ፤ የተጀመሩ ልማቶች እውን የሚሆኑት በአካባቢው ሰላም ሲሰፍንና ለልማት የሚተባበር ሕዝብ ሲኖር መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም ለ2019 የትምህርት ዘመን አስፈላጊ ግብዓቶች መሟላታቸውን ጠቁመው፣ በቀጣይም ተቋሙ ሙሉ አገልግሎት እንዲሰጥ ከማኅበረሰቡና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የመብራት፣ የውኃና የአጥር ሥራዎችን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።
የወልድያ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዱባለ አብራሬ በበኩላቸው አዲሱ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ምቹ በሆነ አካባቢ እንዲማሩና በአካባቢው ያሉ ተፈናቃይ ተማሪዎችን አካቶ ለማስተማር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል። ማኅበረሰቡ ትምህርት ቤቱን የመጠበቅና የመንከባከብ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበው፣ ያልተጠናቀቁ ቀሪ ሥራዎችን ለማሟላት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
በምረቃው ወቅት የክልሉ የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔትና ሥራ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አሰን ሙህዬ እንደገለጹት ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ የትምህርት አካላት የተማሪዎች ወንበር፣ መጽሐፍና መምህራንን የማሟላት ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል። በተጨማሪም ፕሮጀክቱ በገባው ውል መሠረት ቢጠናቀቅም፣ ለተጨማሪ የአጥርና የድጋፍ ግንብ ግንባታ በፕሮፖዛሉ መሠረት ተጨማሪ በጀት ይዞ ለማስገንባት እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎችና ተሳታፊዎች ትምህርት ቤቱ መገንባቱ የተሻለ አመለካከት ያለውና አገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት እንደሚረዳ ገልጸው፣ ቀሪ ሥራዎች በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቁ በመጠየቅ የተገነባውን ንብረት ለመንከባከብ ቃል ገብተዋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የፌዴራል ከተማና መሠረተ ልማት የግዢ ስፔሻሊስት አቶ ይሕነው መንግሥቴን ጨምሮ በርካታ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የአካባቢው ማኅበረሰብ አባላት ተገኝተዋል።

good