በሥነ-ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የቢሮ ኃላፊው ዶ/ር ሞላ መልካሙ እንደገለጹት፤ በተያዘው በጀት ዓመት በክልሉ የሚገኙ ከተሞችን ወደ ተሻለ የዕድገትና የዘመናዊነት ደረጃ የሚያሸጋገሩ በርካታ ትኩረት የሚሹ ተግባራት ተለይተው ወደ ሥራ ይገባሉ ብለዋል።
በበጀት አመቱ የከተሞችን የመሰረተ ልማት ችግሮች ለማቃለልና የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የከተሞችን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ የሚያስችሉ የቤት ልማት ፕሮጀክቶች ተጠናክረው የሚቀጥሉ ሲሆን፣ የከተሞችን ውበትና ምቹነት የሚጨምሩ የኮሪደር ልማት ሥራዎች በስፋት ይከናወናሉ ተብሏል።
በተመሳሳይ መልኩ የከተሞችን የአገልግሎት አሰጣጥ ዘመናዊ፣ ቀልጣፋና ከሙስና የጸዳ ለማድረግ የዲጂታል አሰራር ሥርዓት ሙሉ በሙሉ እንደሚዘረጋና የስማርት ሲቲ አስተዳደርን ዕውን የማድረግ ሥራዎች ልዩ ትኩረት ይሰጣቸዋል።
በሌላ በኩል የከተሞችን የውስጥ ለውስጥ መንገድ፣ የፍሳሽ ማስወገጃና ሌሎች መሰረታዊ የልማት አውታሮችን ይገነባሉ። በተጨማሪም የመሠረተ ልማት ቅንጅታዊ አሰራርን በማሳደግ ከመንገድ፣ መብራት፣ ውሃ እና ቴሌኮም ጋር ከዕቅድ ዝግጅት ጀምሮ በተቀናጀ መልኩ በመስራት ያልተገባ የሀብት ብክነትን ማስቀረት እንደሚያስፈልግ አስምረውበታል።
በከተሞች የሚገኙ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ተጠቃሚ የሚያደርጉ የከተማ ምግብ ዋስትና እና የሴፍቲኔት ፕሮግራሞች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የተገለጸ ሲሆን፣ የአረንጓዴ ልማት ይዞታዎችን ማስፋፋትና የከተሞች የአየር ንብረት ጥበቃ ሥራዎች በልዩ ትኩረት እንደሚሰሩ ተመላክቷል።
ከተሞችን በፕላን መምራት ዋና የከተማ ልማት አቅጣጫ መሆኑን የጠቆሙት ቢሮ ኃላፊው፣ ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራና ግንባታን ከመከላከል አኳያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ያለው ቅንጅት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርተዋል።
በመጨረሻም የታቀዱትን ግቦች ለማሳካትና አፈጻጸሙን በተግባር ለመመዘን ጠንካራ የክትትልና የምዘና ሥርዓት የሚዘረጋ ሲሆን፣ አመራሩና ባለሙያው በዕቅዱ ውል መሰረት እንደሚመዘኑ ተገልጻል። ቢሮ ኃላፊው ዶ/ር ሞላ መልካሙ አጠቃላይ የታቀዱት ግቦች ስኬታማ የሚሆኑት የዞንና የሬጆፖሊታን መምሪያዎች፣ የከተማ አስተዳደሮች፣ ባለድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ በቅንጅትና በባለቤትነት ስሜት ሲንቀሳቀሱ በመሆኑ፣ ለዕቅዱ ውጤታማነት ሁሉም አካል የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

