የአብክመ ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ በስሩ ከሚገኙ ዞኖችና ሪጂዮፖሊታን መምሪያዎች የተወጣጡ የዕቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ቡድን መሪዎች በተገኙበት የ2019 በጀት ዓመት የጋራ ዕቅድ ማናበቢያ መድረክ በባህር ዳር ከተማ ማካሄድ ጀምሯል።

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ሞላ መልካሙ እንደገለጹት፤ በበጀት ዓመቱ የታቀዱ ዋና ዋና ተግባራትን ከላይ እስከ ታች ባለው መዋቅር ዘንድ የጋራ መግባባት በመፍጠርና ወጥ በሆነ አሠራር በመምራት፣ በከተሞች እየጨመረ የመጣውን የኅብረተሰብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ተግቶ መመለስ ያስፈልጋል ብለዋል።

ኃላፊው አክለውም ክልሉ የሚገኝበትን ፈጣን የከተሞች ዕድገት ያገናዘበ ዘላቂ የልማት ስራ መስራት እንደሚገባ ጠቁመው፤ ከተሞችን ለኑሮና ለሥራ ምቹ ለማድረግ ስማርት ሲቲዎችን (ዘመናዊ ከተሞችን) በመገንባት የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ማሻሻል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በ2019 በጀት ዓመት ትኩረት የተሰጣቸው ዋና ዋና የልማት ግቦች መካከል በ85 የከተማ አስተዳደሮች የኮሪደር ልማት እንዲሁም በ19 ከተሞች የ«ስማርት ሲቲ» ትግበራ ይጀመራል ብለዋል። የአንድ ከተማ አንድ ፕሮጀክት፣ የቤት ልማት፣ የጭቃ ቤት ቅነሳ፣ የቀዳማዊ ልጅነት እና የእኛ ትውልድ ከተማ ግንባታ ኢኒሼቲቮች ወደ ሙሉ ትግበራ ይገባሉ ብለዋል።

በሌላ በኩል የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሱለይማን እሸቱ የመድረኩን አስፈላጊነት ሲያስረዱ፤ የዕቅድ ማናበቡ መድረክ በተግባራት ላይ ግልጽነት ለመፍጠርና ጥራቱን የጠበቀ፣ የተናበበ መረጃ ለማዘጋጀት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል። የዘርፉ ባለሙያዎችም የተሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት በመወጣት የጋራ ግቦችን እንዲያሳኩ አሳስበዋል።

በመድረኩ የተሳተፉ ባለሙያዎች በበኩላቸው ቢሮው ለዕቅድ ማናበብ ስራው የሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት አደንቀው፤ በዕቅድ ዝግጅት ወቅት ያጋጠሟቸውን ችግሮች በማንሳት ሰፊ ውይይት ያደረጉ ሲሆን፣ በግንኙነቱም የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ተችሏል።

እስከ ነሐሴ 06/2018 ዓ.ም የሚቆየው ይህ የምክክርና የዕቅድ ማናበብ መድረክ በነገው ዕለትም ቀጥሎ ውይይት ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ዘጋቢ፡ #ሙሉጌታ ስመኝ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top