የአማራ ክልል ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ የ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት የሥራ ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ እና የ2019 ዓ.ም ዕቅድ ትውውቅ መድረክ በባህር ዳር ማካሄድ ጀምሯል።

በሁነቱ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ የቢሮው ኃላፊ፣ የቢሮው ኮር አመራሮች፣ የዞንና ሪጆፖሊታን መምሪያ ኃላፊዎች፣ ከንቲባዎች፣ የቢሮ ዳይሬክተሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።

በዕለቱም የቢሮ ኃላፊው ዶ/ር ሞላ መልካሙ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ በንግግራቸውም ከተሞች የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ማዕከል መሆናቸውን ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት የሚታየው ፈጣን የክትመት ሂደት በአገልግሎት አቅርቦት፣ መኖሪያ ቤትና በመሠረተ ልማት ፍላጎት ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን አብራርተዋል። ይህንን ውስብስብ ችግር ለመፍታትም ተቋሙ የ5 ዓመት መሪ የልማትና መልካም አስተዳደር ዕቅድን መሠረት አድርጎ ወደ ተግባር መግባቱን ጠቁመዋል።

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በቁልፍና አበይት ተግባራት፣ በተለይም በሀገራዊና ክልላዊ ኢኒሸቲቮች በኩል በርካታ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን የቢሮ ኃላፊው በንግግራቸው አብራርተዋል። በዚህም መሠረት የኮሪደር ልማት በ35 ከተሞች ተግባራዊ በመደረጉ በርካታ የመንገድና የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች መከናወናቸውንና ለ180,205 ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል። በተጨማሪም 71,721 መኖሪያ ቤቶች መገንባታቸውን፣ ለ1,248 ማኅበራት የመሬት ርክክብ መደረጉን፣ ከባለፈው ዓመት የተንከባለሉ 93 ፕሮጀክቶች መጠጠናቀቃቸውን እና 557 አዳዲስ ፕሮጀክቶች ፍጻሜ ማግኘታቸውን አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል የተመዘገቡትን ስኬቶች ያህል በሥራ ሂደት ላይ ተግዳሮቶች ማጋጠማቸውን የቢሮ ኃላፊው ገልፀዋል። የዲዛይን ጥራት እጥረት፣ የውልና የመረጃ አያያዝ ጉድለት፣ የግንባታ ግብዓቶች የዋጋ ተለዋዋጭነት፣ ከሌሎች መሠረተ ልማት አቅራቢዎች (መብራት፣ መንገድ፣ ውሃ፣ ቴሌ) ጋር ያለው የቅንጅት ውስንነት እና የፀጥታ ችግሮች ለፕሮጀክቶች መጓተት ምክንያት መሆናቸውን ገልጸዋል። አክለውም በከተሞች የሚታየውን ሌብነት መታገልና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት ልዩ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን አሳስበዋል።

በመጨረሻም ቢሮ ኃላፊው በቀጣዩ የ2019 በጀት ዓመት ትኩረት የሚሰጣቸውን ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ይፋ አድርገዋል። እነዚህም ዲጂታል አሠራሮችን እስከ ታችኛው መዋቅር በማውረድ አገልግሎት አሰጣጥን ማዘመንና ሌብነትን በቁርጠኝነት መታገል፣ ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራና ግንባታን በመከላከል ከተሞችን በፕላን መምራት፣ የኮሪደር ልማትን ጥራት ባለው መልኩ ማስፋፋት፣ ከውሃ፣ መንገድ፣ መብራትና ቴሌ ጋር ከመነሻው በተቀናጀ መልኩ በመስራት የመሠረተ ልማት ቅንጅትን ማሳደግ እንዲሁም የሪል ስቴት አልሚዎችንና ማኅበራትን በመደገፍ የጭቃ ቤት ቅነሳን ማፋጠን ናቸው ብለዋል።

በየደረጃው ከሚገኘው አመራርና ባለሙያ ጋር ውጤት ተኮር የዕቅድ ውል በመያዝ ጥብቅ የምዘና ሥርዓት እንደሚዘረጋ በመግለጽ፣ ይህ የግምገማ መድረክ እርስ በእርስ የመማማሪያ፣ ድክመቶችን በግልጽ የመገምገሚያና ለ2019 ዓ.ም የላቀ ሥራ አዲስ አቅም የምንሰንቅበት እንዲሆን በመመኘት መድረኩ በይፋ መከፈቱን አብስረዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top