“አመራሩና ፈጻሚው በክረምት ወራት የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ላይ ብቻ ከማተኮር ወጥቶ የህዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ እያደረገ ያለው የተግባር ምላሽ አበረታች ነው”

አህመዲን መሀመድ (ዶ/ር)

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪ

አመራሩና ፈጻሚው በክረምት ወራት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ላይ ብቻ ከማተኮር ወጥቶ፣ ከምርጫ ማግስት ጀምሮ ህዝቡ ያነሳቸውን የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች በብቃት ለመመለስ እያደረገ ያለው የተግባር እንቅስቃሴ አበረታች መሆኑን ገለጹ።

​አስተባባሪው ይህንን ያሉት የክላስተሩ ቢሮዎችና የተቋማት ኃላፊዎች፣ ምክትል ኃላፊዎች እንዲሁም የህዝብ ግንኙነት አመራሮች በተገኙበት በተካሄደው የክረምት ወራት የመስክ ሱፐርቪዥን ድጋፍ እና ክትትል እና የ2019 በጀት ዓመት የሁለት ወራት የእቅድ አፈጻጸም የግምገማና የውይይት መድረክ ላይ ነው።

ዶ/ር አህመዲን በመድረኩ መክፈቻ ላይ ለ2019 አዲስ ዓመት ዋዜማ ለጳጉሜ 3 “የጽናት ቀን” እንኳን አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞታቸውን ለተሳታፊዎች በመግለጽ በዛሬው ቀን የሚደረገው መድረክ ልዩ የሚያደርገው የከተማ ልማት ክላስተር ስራዎች ተጨባጭ ውጤት የሚያመጡት የማይወላወል የህዝብና የአመራር መተባበር እና ጽናት ሲታከልበት በመሆኑ፣ አላስፈላጊ ፈተናዎችንና እንቅፋቶችን በጽናት በመቋቋም የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን፣ የሰው ተኮር አገልግሎቶችንና የኢንሼቲቭ ስራዎችን በጥራትና በጊዜው አጠናቆ ለህዝብ ጥቅም ማዋል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

​በግምገማ መድረኩ ላይ እንደተመላከተው፣ በክረምት ወራት በየደረጃው የሚገኙ የዞንና የከተማ አስተዳደር መዋቅሮች የተሰጣቸውን የልማትና የአገልግሎት አሰጣጥ ግቦች ለማሳካት ያሳዩት ቁርጠኝነትና የነቃ ተሳትፎ አበረታች ነው ብለዋል ።

​በተለይም በሰው ተኮር ልማት ስራዎች በርካታ ሞዴል ተግባራት መከናወናቸው ተገልጿል። በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወገኖች ደረጃቸውን የጠበቁ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ የተማሪዎች ምገባ፣ እና ሴቶችን በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶች ስኬታማ በሆነ መንገድ ተግባራዊ መደረጋቸው ለአብነት ተነስቷል። በተጨማሪም የማህበረሰቡን አቅም በማስተባበር የኢንሼቲቭ ተግባራት አበረታች ውጤት እያመጣ እንደሚገኝ ተብራርቷል።

​ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን በተመለከተ የከተማ ልማት ክላስተር ተቋማት የሚከተሉትን ዋና ዋና ተግባራት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ቀርቧል በተለይም የህዝቡን እንግልት የሚቀንሱ ቀልጣፋና ዘመናዊ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቶችን መዘርጋት፤ በሚተገበሩ ኢንሼቲቮ ሥራዎች የህዝብን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን በስፋት በማደራጀት የሥራ ዕድል ፈጠራን ማላቅ፣ ገበያን የማረጋጋት ስራዎችን አጠናክሮ መስራት፣ ከምራች ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት እና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደሚገባ ዶ/ር አህመዲን አሳስበዋል።

የክልላችንን የ25 ዓመት የአሻጋሪ ዕድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ መነሻ በማድረግ የከተማውን ማህበረሰብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በዘላቂነት የሚመልሱ ስራዎችን መስራት እንዲሁም የተቀማት አደረጃጀትና የተቀናጀ አሰራር ተግባራዊ እንዲሆን ለታችኛው መዋቅር አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ ማህበረሰቡ በልማትና በዘላቂ ሰላም ግንባታ ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን በትኩረት እንደሚሰራና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በተደራጀ አግባብ ደረጃ በደረጃ እንደሚፈቱ ተመላክቷል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top