በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በፋሲሎ፣ በየካቲት 23 እና በዶና በር ትምህርት ቤቶች ያስገነባቸውን 5 ብሎክ 20 አዳዲስ የቅድመ 1ኛ ደረጃ ት/ቤቶችን ገንብቶ አስመረቀ፡፡

በምርቃ ፕሮግራሙ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ ሞላ መልካሙ (ዶ/ር) እንደገለጹት የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔትና ሥራ ፕሮጀክት ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል የአነስተኛ ማኅበራዊ ተቋማት ግንባታ የሚጠቀስ ሲሆን እንደ ክልል 73 የመማሪያ ክፍል የተገነቡ ሲሆን የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የምግብ ዋስትና እና ሴፍቲኔት ጽ/ቤት 5 ብሎክ 20 ክፍሎችን የያዘ ት/ቤት ተጠናቆ መመረቁ ለህጻናት ምቹ የመማር ማስተማር ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በዚህ ዘርፍ 6 የሸድ ብሎክ 254 ክፍሎች፣6 አነስተኛ የህዝብ መዝናኛ ፓርክ፣ 4 የህዝብ መጸዳጃ ቤት ግንባታዎችን በማከናወን ሁሉን አቀፍ የከተማ ልማት ላይ እያበረከተ ይገኛል ያሉት ዶ/ር ሞላ መልካሙ በአጠቃላይ በአነስተኛ ማህበራዊ ተቋማት ግንባታ በጀት ከ72ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ተደርጓል ብለዋል፡፡

የባሕርዳር ከተማ ከንቲባ የተከበሩ አቶ ጎሹ እንዳላማው በበኩላቸው እንደገለጹት ትምህርት ለሀገር ልማት የጀርባ አጥንት ነው ያሉ ሲሆን በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም የአፀደ ህፃናት ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ተማሪዎች ሲመጡ ናፍቋቸውና ወደውት የሚማሩባቸው ውብ፣ ጽዱና ማራኪ የማድረግ ሥራ በትኩረት መከናወኑን ገልፀዋል።

የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ነዋሪዎችን በቀጥታ በገንዘብና በሥራ ዕድል ከመደገፍ ባለፈ፣ በሕዝብ ተሳትፎ አማካኝነት እንደ ትምህርት ቤት፣ ጤና ጣቢያና የአረንጓዴ ልማት መሠረተ ልማቶችን በመገንባት የከተማን ገጽታ ለመቀየር በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል ብለዋል ከንቲባው።

ከተማ አስተዳደሩ በቀጣይ በጀት ዓመት በቀጥታ በጀት መድቦ የተሻሉ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ማቀዱን የገለጹት ክቡር ከንቲባው የመማሪያ ክፍሎችንና ቤተ-መጻሕፍትን በማዘመን እንዲሁም ስማርት ክፍሎችን በመፍጠር ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆኑ ተማሪዎችን ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የባሕርዳር ከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ እመቤት መንግስቱ፤ ልማታዊ ሴፍቲኔት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ የዜጎችን ኑሮ በመቀየርና የከተማዋን ገጽታ በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል። በዛሬው ዕለት በሦስት ትምህርት ቤቶች የተገነቡ 5 ብሎኮች እና 20 የመማሪያ ክፍሎች ተጠናቀው ለመማር ማስተማር ክፍት መደረጋቸውን ኃላፊዋ ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡ ሙሉጌታ ስመኝ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top